በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በቀጠለው የቫሊዴሽን ወርክሾፕ የማኔጅመንት፣ የአመራር እና የአስተዳደር ኮሌጅ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱን አስገመገመ፤
በኢፐሰዩ የማኔጅመንት፣ የአመራር እና የአስተዳደር ኮሌጅ College of Management, Leadership & Governance (CMLG) በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሰጡ ከተመደቡለት የትምህርት ፕሮግራሞች መካከል በአራቱ ኮርሶች ላይ የሰበሰበውን የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት፣ ጥር 1 ቀን 2018 በስልጠና ኢንስቲትዩት በተካሄደው Validation ወርክሾፕ ላይ አቅርቦ አስገመገመ፡፡
የዳሰሳ ጥናቱን ካካሄዱት ለየኮርሱ የተዋቀሩት የኮሚቴ አባላት ሲሆኑ፣ ለዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱ ግብአት የሚሆን መረጃ ከአዲስ አበባ እና ከክልል መንግስታት ባለድርሻ አካላት እና ኬሌሎች ሴክተሮች በተሰበሰበ መሆኑ በሪፖርት አቅራቢዎቹ ተገልጿል፤ ሪፖርቱ ከመነሻው እስከ ጥናቱ ማጠቃለያ የነበረውን ሂደት ያካተተ ሲሆን፣ የህዝብ አስተዳደር እና አመራር ትምህርት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በዶ/ር መልካሙ ሞሻጎ፣ የህዝብ ፖሊሲ ጥናት ትምህርት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በዶ/ር ንጉሴ ዳባ፣ የማናጅመንት ትምህርት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በዶ/ር ገብሬ ሶርሳ እና የልማት አስተዳደር ትምህርት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በዶ/ር ታዬ ዓለሙ በኩል ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሰብሳቢዎቹ ለቀረቡት ሀሳብ እና አስተያየቶች በሪፖርት አቅራቢዎቹ እና በኮሚቴው አባላት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ ጥናቱ በተሰጡት ሃሳብ እና አስተያየቶች ዳብሮ፣ በኮሌጅ ደረጃ እንደሚጸድቅ እና ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡