የኢፐሰዩ የሪፎርም አደረጃጀት ግብረ-ኃይል የስራ ፍሰት ግምገማ የመጀመሪያ ሪፖርቱን ለዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላት አቀረበ፤
የኢፐሰዩ የሪፎርም አደረጃጀት ግብረ-ኃይል የስራ ፍሰት ግምገማ የመጀመሪያ ሪፖርቱን ለዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላት አቀረበ፤
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ተከትሎ፣ አደረጃጀቱን ለማስተካከል ያቋቋመው ግብረ-ኃይል፣ በነባሩ የስራ ፍሰት ላይ ያካሄደውን ዝርዝር የግምገማ ሪፖርት፣ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ/ም በህዳሴ አዳራሽ አቀረበ፡፡
ሪፖርቱ በአካዳሚክ እና በአስተዳደር የስራ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ ነባር የስራ ፍሰቶችን በጥልቀት የፈተሸ መሆኑ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፤ የካውንስሉ አባላት ለተሰራው ስራ ያላቸውን አድናቆት እየገለጹ፣ ቢጨመር እና ቢስተካከል መልካም ነው ያሉትን ገንቢ ሀሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል፤ በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) ግብረ- ኃይሉ ለሰራው አመርቂ ስራ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ “የዚህ ግብረ-ኃይል አባላት ከቤተሰባቸው ተለይተው እና በማይመች ሁኔታ እስከ ምሽት አራት ሰዐት ድረስ እየሰሩ ላመጡት አመርቂ ውጤት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡ አስከትለውም፣ የሪፎርም ዓላማ የተቋሙን ተልእኮ በውጤታማ መንገድ ማሳካት መሆኑን ገልጸው፣ “ውጤታማ ሪፎርም ለማካሄድ አሁን ላይ ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ እና ነባሩን የስራ ፍሰት መፈተሸ አስፈላጊ ነው፤ ግብረ-ኃይሉ ዛሬ ያቀረበው ሪፖርት የስራውን ፍሰት በአግባቡ በመገንዘብ ችግሮቹን መለየቱን በግልጽ ያሳያል፤ ይህንን በአግባቡ ተገነዘብን ማለት በቀጣይ የምንሰራውን የሪፎርም ስራ ውጤታማ እንደሚያደርግልን መረዳት ይቻላል፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የግብረ-ኃይሉ አባላት ሪፖርታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ለዛሬው ስራ መሳካት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ያደረጉት ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል ትልቅ ድርሻ እንደነበረው በመግለጽ አመስግነዋቸዋል፡፡
Visit our website: https://www.epsu.edu.et/user
Follow our Facebook page: https://web.facebook.com/EPSUfb
Follow our Telegram Channel: https://t.me/epsutelegram
PR call: 0945746405