በኢፐሰዩ የሪፎርም ሥራዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መድረክ ተካሄደ
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢፐሰዩ) እየተካሄዱ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን አስመልክቶ ለዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መርሀ-ግብር ታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ ተደረገ፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ሠራተኞች፣ አመራሮችና እና ሰራተኞች እንዲሁም የአስተዳደር ዘርፍ አመራሮችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
በመርሀ-ግብሩ ላይም በዩኒቨርሲቲው እየተካሄዱ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት በዶ/ንጉስ ታደሰ፣ የተሸሻለው የፕሮጀክት ስራዎች አስተዳደር መመሪያ በዶ/ር አለማየሁ ደበበ፣ የዩኒቨርሲቲው የአምስት ዓመት (2019-2023 ዓ.ም) ስትራቴጂክ ዕቅድ በዶ/ር አምሳሉ በደሞ እንዲሁም የተሸሻለ የአካዳሚክ የአመራር ምልመላና መረጣ መመሪያ በዶ/ር ምስጋናው ክፈለው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በዩኒቨርሲቲው እየተካሄዱ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን አስመልክቶም ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ባቀረቡት ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው ከተያዙት የሪፎርም ስራዎች መካከል ተጠናቀው ወደ ትግበራ ምዕራፍ የተሸጋገሩ ፣ በቶሎ መጠናቀቅ የሚገባቸው እና ሊጠናቀቁ የደረሱ የሪፎርም ስራዎችን በዝርዝር አቅርበው፣ ሁሉም የሪፎርም አጀንዳዎች ተጠናቀው ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባት እንሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡ በአዲስ መልክ እየተደራጁ ያሉ የሀብት ማፍርያ ስድስት ኢንተረፕራይዞች ጥናት በመካሄድ ላይ መሆናቸውን እና በዩኒቨርሲቲው ትልቁ ሪፎርም የሥርዓተ- ትምህርት ክለሳና ቀረጻ ሪፎርም በመሆኑ በትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳና ቀረጻ ስራዎችም በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ንጉስ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
አክለውም የተጀመረውን የለውጥ ሥራ በርብርብ ከዳር ማድረስ እና ማጠናቀቅ፣ መደበኛ የትምህርት፣ የስልጠናና የምርምር ስራ መገምገምና ወደ ተግባር መግባት እንዲሁም ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን በልዩ ሁኔታ ትኩረት በመስጠት መተግበር ላይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የራሱን ኃላፊነትና ድርሻ በመወጣት ዩኒቨርሲቲው የያዘውን የለውጥ አጀንዳ ከዳር ለማድረስ መትጋት እንደሚገባው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በማስከተልም በተሸሻለው የፕሮጀክት ስራዎች አስተዳደር መመሪያ ሪፖርት ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩና ከምርምር በጀት አሰጣጥና የአከፋፈል ሥርዓት ጋር ተያይዘው፣ በተመራማሪዎች ዘንድ ቅሬታ ይነሳባቸው የነበሩ ጉዳዮች ላይ የተደረገው ማሻሻያ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድም ሰፊ ጥናት ተደርጎበት በስድስት ስትራቴጂያዊ ጭብጦችና በአስራ ሰባት ግቦች ተለይቶ የተዘጋጀ መሆኑ፣ እንዲሁም የተሸሻለ የአካዳሚክ የአመራር ምልመላና መረጣ መመሪያም ወደ አመራርነት የሚመጡ ሰራተኞች የሚመዘኑት የብቃት አሀዶችን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆኑንና ምልመላዉም ተጨባጥ መለኪያዎችና መስፈርቶችን ያካተተ መሆኑ በቀረቡት ሪፖርቶች ተገልጸዋል፡፡
በሪፖርቶች ላይም የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶች ከቤቱ የቀረቡ ሲሆን፣ ለቀረቡት ሀሳብና አስተያየቶችም ከመድረክ ምላሽና ማብራሪዎች ተሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ንጉስ ታደሰ በሰጡት ማጠቃለያ መድረኩ የተዘጋጀው እየተካሄደ ባለው የለውጥ ሥራ ላይ ግልጽነት ለመፍጠና ግብዐትን ለማሰባሰብ መሆኑን ጠቅሰው፣ አጠቃላይ ዕቅዱም ዩኒቨርሲቲውን በመለወጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዩኒቨርሲቲ የማድረግ አላማን ያነገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም “አሁን እየሰራን ያለነው ቀደም ሲል መሰራት የነበረበትን ሥራ አሁን መስራት ካለብን ስራ ጋር ደርበን፣ እንዲሁም ለወደፊቱ ልንሰራው የሚገባንን በአንድላይ እየሰራን በመሆኑ ጫና ቢፈጥርም፣ ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን፣ እንዲሁም የተቋሙን ህልውና ለማስቀጠል ስንል፣ ሁላችንም ያለብንን ድርብ ኃላፊነት ለመወጣት በማይመች ሁኔታ ውስጥ እንኳን ብንሆን ትልቁን አላማ በመያዝ ተግተን መስራት እና ተቋማችንን መለወጥ፣ እንደ ሀገርም የድርሻችንን መወጣት ይገባናል፡፡” ብለዋል፡፡