በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፍላጎት ዳሰሳ ወርክሾፕ ተካሄደ
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢፐሰዩ) የከተማ ጥናት ኮሌጅ (College of Urban Studies /CUS) በመጀመሪያ ዲግሪ ሊሰጥ ለታቀደው የአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ (Environmental Science) መርሐ-ግብር በተካሄደው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት መሰረት፣ ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም የግብአት ማሰባሰቢያ ወርክሾፕ ተካሄደ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ዲን ደጉ በቀለ (ዶ/ር) በኮሌጁ ለሚከፈቱት ስድስት የትምህርት መርሐ-ግብሮች ከሁለት ወር ለበለጠ ጊዜ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን እና ከታህሳስ 13 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት እየቀረበ፣ ግብአት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ “ዛሬ የሚቀርበው የአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ (Environmental Science) መርሐ-ግብር የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ሊከፈት የታቀደ አዲስ የትምህርት ክፍል ስለሆነ ሁላችንም በንቃት ተወያይተን አስፈላጊውን ግብአት መስጠት ይኖርብናል፡፡” በማለት አሳስበዋል፡፡
ቀጥሎም፣ ከሁለት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ ሲካሄድ የነበረው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት የጥናት ኮሚቴው አባላት በሆኑት በዶ/ር ምትኩ አዲሱ እና በዶ/ር መኮነን ማስቻል በኩል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ የወርክሾፑ ተሳታፊዎች፣ በከተማ ጥናት ኮሌጅ በተለያየ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራን እና ተመራማሪዎች፣ ከሌሎች ኮሌጆች የተጠሩ የዘርፉ ምሁራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች እና ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ሲሆኑ፣ ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ጥናቱን የሚያበለጽግና እና ለቀጣዩ ስራ ግብአት የሚሆን ገንቢ ሀሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ (Environment and climate change) የትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ትግዛው ላመስግን (ዶ/ር)፣ የትምህርት ክፍሉ መከፈት ለፐብሊክ ሴክተሩ ብሎም ለሀገሪቱ የሚሰጠው ፋይዳ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- ሀገራችን ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ እና ከግሪን ሀውስ ኢሚሽን ጋር የተያያዙ አለም አቀፍ ስምምነቶችን መፈረሟን እና የፓሪስ ስምምነትም አባል መሆኗን አስታውሰው፣ “ከሁሉም በላይ የግሪን ሌጋሲ ፖሊሲዎች እና እስትራቴጂዎችን ቀርጻ በስፋት የምትንቀሳቀስ ሀገር በመሆኗ፣ ፖሊሲዎቿን እና እስትራቴጂዎቿን ለማስፈጸም ሆነ በዘርፉ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች ለመተግበር እንድትችል፣ በርካታ በአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ (Environmental Science) እውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ያስፈልጓታል፤ ስለዚህ የትምህርት ክፍሉ መከፈት ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡” በማለት የትምህርት ክፍሉ መከፈት የሚኖረውን ፋይዳ አብራርተዋል፡፡
ኮሌጁ ከታህሳስ 13 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ፣ በከተማ ፕላኒንግ እና ዲዛይን ትምህርት ክፍል፣ የከተማ መሬት ማናጅመንት ትምህርት ክፍል እና በቋሚ ንብረት ትመና ትምህርት ክፍሎች ተመሳሳይ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በማዳመጥ ግብአት የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም ከተሰብሳቢዎቹ ለቀረቡ ጥያቄ እና አስተያየቶች ማብራሪያ ተሰጥቶ መርሐ- ግብሩ ተጠናቋል፡፡